የችግር መፍትሄ የሚመነጨው ከግልሰብ እንጂ ከቡድን አይደለም በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ ልዩ የለውጥ ሞገድ እያየን እንገኛለን። ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ሚሊዮኖችን ያማለለ ንግግርን እና ዕቅዳቸውን ለህዝብ በማሰተዋወቅ ላይ ናቸው። ስልጣን ከያዙበት ቀን ጀምሮ እየተገበሩት ባለው ፈጣን የስራ ክንውን ከተማረኩት ሚሊየኖች ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ። የዚህም ክንውኖች ቁንጮ የሆነው ሀገራዊ ዕርቅ እና የአንድነት ጥሪ ልዩ ስፍራ የተሰጠው ጉዳይ ሆኗል። ለዛሬ ግን የማካፍለው ሃሳብ ወጣቶችን በቡድን ሳይሆን በግል የማነቃቃት አስፈላጊነት ምክንያቶችን ስለማሳየት ይሆናል። በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ልዩ ልዩ የወጣቶችን እንቅስቃሴ እየተመለከትኩኝ ነው። አዲስቷ ኢትዮጵያ እኔ ነኝ የሚለው በማህበራዊ ድህረ ገፅ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ጭምር የተሳተፉበት እንቅስቃሴ ልዩ ትኩርት ሰጥቼዋለው። ርዕሱ እጅግ የሚማርክ እና የጊዜው መልክት ነው ብዬ አምናለው። ይሁንና የሰማኋቸው ንግግሮች ሁሉ (ያልሰማኋቸው ደግሞ ንግግርች ደሞ ሊኖሩ ይችላሉ) በህብረ ቡድን መዋቅር ላይ የሚያተኩሩ ይመስላሉ። ይህ ማለት ወጣቶችን በአንድ ላይ በቡድን በቡድን የማየቱ ነገር ከፍ ያለ ስፍራ የተሰጠው ጉዳይ ሲሆን ይታያል። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዜና ላይ የተመረቁ ተማሪዎች ተደራጅተው የኮብል ስራ መስራት ጀመሩ የሚለውን ዜና ስሰማ በጣም ነው ማመን ያቃተኝ። ስራ መናቄ አይደለም። ማንም ሰው ራሱን ለመደገፍ የትኛውንም ስራ ትንሽ ወይም ትልቅ ሳይል መስራት አለበት። ነገር ግን ልቤን የከበደው “አራት አመት በዩንቨርስቲ የተማሩ ተማሪዎች ተድራጀተው” የሚለው አረፍተ ነገር ነው። ምክንያቱም እኔ ዜናውን የተረዳሁት ድህነቱ አስገድዷቸው አልያም ከመካከላቸው በተማሩበት ሙያ ሌላ ስራ እንዴት መስራት እንደሚችሉ ማየት አልቻሉም። ወይም ጥሩ በእድሜ የገፋ ጠቋሚ አልነበረም ብሎ ማሰብ ይቻላል። ሪፖርቱ በዛ መንገድ ቢቀርብ ኖሮ ጥሩ ትምህርት ይሆን ነበር። ነገር ግን የአራት ዓመት የከፈተኛ ትምህርት ግብ የኮብል መንገድ ስራ ላይ መደራጀት ከሆነ የትምህርት ተቋሙ ዓላማም ያጠያይቃል። ከዛ ባሻገር ሁሉ ነገር አንድ ለአምስት ተደራጅ፤ ቤት እንድትሰራ ተደራጅ፤ገንዘብ እንድትበደር ተደራጅ፤ ዲያስፖራው ይደራጅ የሚለው ሃሳብ እጅ እጅ ብሎኛል። በመሆኑም ይህ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እኔ ነኝ የሚለው ሃሳብ “እኛ” ከሚለው ሃሳብ የሚያወጣ እና እያንዳንዱ ሰው በተሰጠው የህይወት ዘመን “የእኔ” ድርሻዬ ምንድ ነው? የሚለውን ሃሳብ ኢንዲያስብ ፍንጭ ይሰጣል ብዬ አስባለው። ይህን "አዲሲቷ ኢትዮጵያ እኔ ነኝ" የሚለው ከአባባል እና ከጊዜያዊ ዕርቅ የዘለለ መሆን አለበት። ስሜታችን ተስፋ ስለሞላው የሚቀየረው ስሜታችን ብቻ ነው። ነገር ግን ያ የግል ተስፋ በተግባር መልካም ዓላማን በማስፈፀም ሲለወጥ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እኔ ነኝ የሚለው ትርጉም ያገኛል። ታሪክን ስንመለከት ቡድን እንደ ቡድን የማስፈፀም ቅልጣፌን እንጂ ችግር የመፍታት ግኝትን አያመነጭም። በቡድን የሚሰጥ የውሳኔ ሃሳብ አለ እንኳን ቢባል አንድ ግለሰብ ከቡድኑ ውስጥ ሃሳቡን መጀመሪያ ሊያፈልቅ ግድ ይላል። ለዚህ ብዙ ምሳሌ መስጥት ይቻላል ይህ ድህረ ገፅ ወደ መቶ የሚጠጉትን ግለሰቦች በሁሉም የህይወት ዘርፎች ዘርዝሮአቸዋል። ባህላችንን ያየን እንደሆነ የተለየ ሃሳብ አንወድም ወይም አናበራታታም። አንድ ሰው በሃሳቡ ቢለይ ይገለላል። በንግግር ውስጥ ክርክር ሲሆን ወድያው ወደ ግጭት እናመራለን። ምክንያቱም ሃሳቡን ከግለሰቡ ለይተን ማየት አንችልም። ይህ የሆነው ብዙ ነገራችን የጋራ ኑሮ ነው በግል ብዙ ሃሳብ የለንም። ነገር ሁሉ በዕቁብ እና በዕድር መሳይ ቡድኖች እንዲያልፍ ይፈለጋል። ይህ ደግሞ ሃሳቦችን ወደ መደጋገም እንጂ አዲስ መፍትሄ አፍላቂዎች አላደረገንም። አንዳንዴ ገጥሟችሁ አያቅም? ልዩ ሃሳብ ይዛችሁ የመንግስት ቢሮ ስትቀርቡ ይህ ጉዳይ አይታወቅም፤ ወይም አይመለከተንም፤ ኮሚቴው ተነጋግሮ ምላሾች ሊሰጥ ይችላል የሚሉ ምላሽ በብዛት ይሰተዋላሉ። ምላሽም በድፍረት የሰጡ ግለሰቦች ይበጠለጠላሉ። ለምሳሌ አርከብ ዕቁባይ በአዲስ አበባ ከነቲባነቱ ብዙ ለውጥ ያመጣ መሪ ነበር። ነገር ግን እንደምሰማው ነበረ የተባለውን ቡድን ሸፈነ መሳይ ምክንያት ተሰጥቶት ከስራው ገለል ተደርጓል። ወይም እርሱ ይህን ያን ቡድን አይወክልም በሚል ተፈርጆም ሊሆን ይችላል የተነሳው። ይህም የሆነው መሪዎች በቦታቸው ቡድንን ወክለው እንጂ በግል አምነውበት ላይሆን ይችላል አመራር የሚሰጡት ማለት ነው። ነገር ግን መሪዎች በግላቸው አቅም የተሰጣቸው እና የሰለጠኑ ቢሆኑ ኖሮ አዳዲስ ነገሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ስጋቶችን መጋፈጥ የሚችሉ ይሆኑ ነበር። የችግር የመፍትሄ ሃሳብ በቡድን አይመነጭም። ሃሳብን ማጎልበትም ሆነ መፈፀም ከማመንጨት ይለያል። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ይባል አይደል ተብዬ ልጠየቅ እችላለው። ነገር ግን ያ አባባል በኢትዮጵያኖች ሲመነጭ ዕድር ተኮር ችግሮችን ለምፈታት እንጂ ገብሬውን በበሬ ከማረስ አላሳረፈውም። ጠበአጭሩ ራዕይ ወይም የችግር የመፍትሄ ሃሳብ በቡድን አይመነጭም። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ይባል አይደል ተብዬ ልጠየቅ እችላለው። ነገር ግን ያ አባባል በኢትዮጵያኖች ሲመነጭ ዕድር ተኮር ችግሮችትን ለምፈታት እንጂ ገበሬውን በበሬ ከማረስ አላሳረፈውም። አንድ ጊዜ በገጠር የሚኖር ገበሬ ቄስ አያቴን ጥያቄ ጠየቁት። እስካሁን በሞፈር ቀንበር ስታርስ ለምን ይህን ነገር በሌላ አልቀይረውም ብልህ አስበህ ታውቃልህ ስለው የአያቴ ምላሽ ፈጣን ነበር። ለምን ብዬ አለኝ ምክንያቱም ሁሉም ገበሬ በዚህ ነው የሚያርሰው ብሎ ጨረሰው። አያችሁ የሱ አመለካከት የተቃኘው ተጋግዞ እርሻን ማረስ፤ ማረም እናም ደግሞ የለውን ትንሽ ነገር መከፋፈል እንጂ ተለይቶ የስራ ጫናውን የሚያቀልለትን ሃሳብ የሚያመንጭበት ዕድል ባህሉ አልፈቀደለትም። የተማርን ነን የምንለውም ያው ነን። በግላችን ባለን ዓላማ ሳይሆን የቡድን ሃሳቦች ይጨፈልቁናል። ችግርን ተቀብለን እንድንኖር አካባቢያችን ያስተምረናል። ጠ/ሚ ዶ/ር አብይን እንዲህ ፍንትው ብለው የወጡት የቡድን ሃሳብ ስለያዙ ሳይሆን የግላቸው ሃሳብ አጉልተው በማሳየታቸው ነው። የሁላችንንም ቀልብ ስበዋል። በመሆኑም ወጣቶች ምን በጋራ እንስራ ወይም ከማን ጋር ልስራ ብሎ ከመጠየቅ በፊት እኔ በግሌ ምን ላድርግ የሚለውን ጥያቄ ቢያስቀድሙ መልካም ነው። ይህ ጥያቄ ሲቀድም ወጣቶች በግላቸው አሰላለፋቸውን ማወቅ ይችላሉ። ከሌላውም ጋር እንዴት በሽርክና መስራት እንዳለባቸው ያውቃሉ። ይህን በሌላ ፁሁፍ እመለስበታለው። እኔ የተመረኩት በሐዋሳ ዩንቨርሲ ኮሚፒተር ሳንይንስ ነው። አስራ ሁለተኛ ክፍል ላይ ሳለው ነበር ምን መማር እና መስራት እንዳለብኝ ያወቁት። ትዝ ይለኛል የሚያበላ ትምህርት ተማር፤ ዶ/ር እገሌ ይህን ያህል ብር ይከፈለዋል አንተም እንደሱ ተምረህ ብር ታገኛለህ ተብዬ በተደጋጋሚ ተነግሮኛል። ነገር ግን ያን መንገድ አልሄድኩም። ብሎም በሙያዬ ወደ ማስበው የመንፈሳዊ አገልግሎት ስራ ለመጀመር ከ ኢትዩጵያ ቴሌኮሚንኬሽን ስለቅ ዕብድ ያለኝ ሰው ጥቂት የሚባል አልነበረም። ታዲያ ያኔ የሰዎችን ጫና ብሰማ ኖሮ ይህን ማድረግ የምችል ይምሰላችሁ ነበር? በፍፁም ለተገለጠልኝ ሃሳብ ራሴን ሰጠሁ አንድ ባንድ ነገሮች እያደጉ እያደጉ አሁን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ብዙ ሃገሮችን የድጅታል ስትራቴጂ ስራዎችን አመራር እሰጣለው። በዚህ ሂደት ውስጥ የጥቂት ግለሰቦች የሞራል ድጋፍ እና ፀሎት ትልቅ ደጀን ሆኖልኛል። የአንድ ግለሰብ ድምፅ ትልቅ አቅም አለው። ማስተጋባት ቀርቶ ተወዳዳሪ የሌለው ሃሳብ በግል እናመንጭ አስተውላችሁ ከሆነ የኢትዮጵያ የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ተደራሹ ቡድን ነው እንጂ ግለሰብ ሲሆን ብዙ ጊዜ አይታይም። ሁሌም ይህ ቡድን እንዴት ይሳተፍ፤ ይምጣ፤ ይቁም ነው እንጅ ስለ እኔ፤ አንተ፤ አንቺ የሚል ንግግር አሁንም ባዕድ ነው። ይህን ለማነፃፀር አንድ የምዕራብ ሚዲያ እና የኛን ሚዲያ የፖለቲከኞች የፖሊሲ አገላለፅ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ይህን የምለው ለማበላልጥ ሳይሆን ልዩነቱን በደንብ እንድታዩ ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ አብዛኛው ህጎች ሲረቀቁ እንዴት አንድ ግለሰብን ይጠቅማሉ ወይም ይጎዳሉ በሚል ክርክር ይደርግባቸዋል። ያንንም ፖሊሲ ተጠሪ አንድ ግለሰብ ነው የሚሆነው። የአሜርካ ፕሬዘዳንቱ ጭምር አንዳንዴ የሚሰጡት ምሳሌ የአንድ ሰውን ታሪክ ውጤት የሚያሳዩ ናቸው። በመሆኑም ፖሊሲውን የሚሰማ ሁሉ እንዴት ያ አዲስ ፖሊሲ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርበት ማወቅ ይችላል። በቅርቡ ደግሞ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ የአርቲስት መሰረት መብራቴ ስም በመጥቀስ እንዴት የእርሷ ተሳትፎ በሁለተኛ ደረጃተማሪዎች ላይ መልካም ተፅዕኖ ሊያመጣ እንደሚችል ግሩም ምሳሌ አስቀምጠዋል። ይህ ችግር ምናልባት አንድ ሰው ውስጥ ያለውን አቅም ያለማወቅ አልያም የባህላችን መጥፎ ተፅኖ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ መደመር የሚለው ሃሳብ የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ የተወደደ ሃሳብ ነው። እኔም አምንበታለሁ። ይህንንም ስል ስለ አንድነት እያሰብኩኝ እንደሆነ ይታሰብ። ነገር ግን መደመር ማለት የእኔ የግል እና ልዩ የሃሳብ መለያን ከሌላው ጋር መጨፍለቅ አይደለም። ይህ ማለት ቁጭ ብዬ የሚሆነውን መመልከት ማለት አይደለም። እንዲያውም እኔ በግሌ ምን ማድረግ እችላለው የሚለወን ጥያቄ በመጠየቅ ልዩ ልዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን የማመንጨት ዕድል እንደተከፈተልኝ አያለው። መደመር የሚለው ለቡድን እና ብሔር ተኮር የሆነ አስተሳሰብን ለማስታረቅ ይጠቅማል ብዩ አስባለው። ነገር ግን የግል ሃሳብን አመሳስሎ መደመር ችግር ያመጣል። ይጨፈልቃል። የግለሰቦች መብትም ሊጣስ ይችላል ብዬ እሰጋለው። ስለዚህ መደመር የሚለው ቃል መዳረሻነቱ የግለሰብ ተሳትፎን የሚያጎለብት እንጂ የሚጨፈልቅ እንዳይሆን ልብ ሊባል ይገባል። ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ይህንን በፓርላማ መደመር ማለት መመሳሰል እንዳልሆን ማብራራታቸውን አስታውሳለው። ለስራ የማስፈፀም ሂደት ስንሰበሰብ ትኩረቱ በታወቀ ዓላማ እና የግል ተሳትፎ በግልፅ በተቀመጠበት ጉዳይ መሰባሰብ ብቅርቡ ወዳጆቼ እስቲ እንቀበጣጥር (brainstorming) እንዴት ሃገራችንን እንደምንጠቅም የሚል ግብዣ አቀረቡልኝ። ልቤ በጣም ደስ አለው። ቀጥዬም ጥያቄ አቀረብኩኝ ምንድ ነው ያሰባችሁት ነገር ወይም ራዕይ ወይም የታሰበ እቅጣጫ ብዬ ጠየኩኝ እናም መልሱ አይ አብረን እንድናፈልቀው ነው ተባልኩኝ። ይህ መተባባር ያለ ትኩረት አቅጣጫ የትም አያደርሰንም ነበር የኔ መልስ። እያንዳንዳችን ውስጥ ልዩ ተሰጦ እና አቅም አለ። ያንን ደግሞ ማወቅ፤ማሳደግ እና ሌሎች ሊከተሉት የሚቸሉት ሃስብ አድርጎ የማውጣት ሃላፊነት የዛው የግለሰቡ መሆን አለበት። መፅሐፍትን ማንበብ አጋዥ ጠቋሚ ግለሰቦችን ከጎን ማሰልፍ ለዚህ ዕገዛ ሊያደርግ ይችላል። በመጨረሻም የግል ሃሳቦች ተቀባይነት እያገኙ ሰዎች በጋራ የግል ሃሳብን የማንሸራሸር ልምድ ሲያሳድጉ ዘረኝነቱም ይቀንሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለው። ብዙ ሰው ስለ ብሔሩ ጭንቅ የሚለው የሚበላው የሚጠጣው በቡድን ሰለሆነ ነው ብዬ አስባለው። በቡድን ተራም ሆነ ቁም ነገር ሃሳቦች በዓይምሮ ይቀረፁና ግንፍል በሚለው ሲሜት አጀብ ተብሎ ስራ ሊሰራ ይሞከራል። ሳይሆን ደግሞ ሆ ተብሎ ለጥፋት ይወጣል። የግለሰብ ልዩ ልዩ ሃሳቦች ተጨፍልቀው ይደመሩና ብዙ የመፍትሔ ሃሳቦች ያለምንም ጥቅም ወደ አፈር ይወርዳሉ።
አደገኛ እና ጎጂ የግል ሃሳብችም ይኖራሉ። እነዚህንም በተቻለ መጠን ሃሳቡን ከግለሰቡ በመለየት የመቋወም ባህላችንን ማሳደግም ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ሌላውን በሚቀጥለው ፅሁፍ ላቅርብ••. ለረዥም ፁሁፍ እና የፊደል ግድፈት ይቅርታ እየጠየኩኝ እስቲ ምን ትላላችሁ የግላችሁ ሃሳብ በሐገር ላይ ምን ፋይዳ ሊኖረው ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ? እንደ ግለሰብ ይህን የምትግልፁብትስ መድረክ ልምዳቹ ምን ይመስላል። ከእያንዳንዳችሁ ለምስማት እናፍቃለው
Sami Tura
7/8/2018 10:39:45 pm
መደመር አንድነትን፣ መጨመርን፣ መያያዝን ያሳያል። ይህ ደ'ሞ ለምንመኛት አዲሲቷ እትዮጵያ እውን መሆን ድርሻው የጎላ ነው። ሀሳብ እና አስተሳሰብ ግን በተለይም ደ'ሞ ከግለሰብ የመፍትሄ አመንጪነት አንፃር መደመር ግዴታቸው አይደለም። የአስተሳሰብ ማህበር የለም የግለሰቦች እንጂ።
Kibrom Tadesse
7/9/2018 12:47:49 am
በጣም መልካም ሃሳብ ነው ያካፈልከው፤ ከዩንቨርስቲ ጀምሮ የራሳችንን ሃሳቦች ማጎልበት ባለብን ጊዜ ብዙዎቻችን በጓደኞቻችን ተቀባይነት ለማግኘትና እንዳይሾብን ተመሳስለን መኖርን እንመርጣለን፡፡ ይህ ግን ጎጂ ነው፤ ማንንም አያሳድግም፤ አንዱ የመደመር ትርጉም ሁሉም በግል ሃሳቡ ተከብሮ መቀባበል ነው፡፡ የመንጋ አስትሳሰብ ይብቃ! 7/9/2018 01:03:15 am
ክብሮም፥
ይኄይስ አማረ
7/9/2018 01:36:01 am
እኔም እንዲሁ ከመንስት ሥራ የዛሬ1 3ዓመት በገዛ ፈቃዴ ስለቅ ብዙ ሰዎች ቤተሰብን ጨምሮ ከሰራሁባቸው17ዓመታት ጋር በማነፃፀር ስለጡረታ ትቶ መውጣት አበክረው ይጠይቁኝ ነበር ::አሁን ላይ የወሰንኩት ውሳኔ ጥሩ እንደነበር እነዚያ ጓደኞችና ቤተሰቦቼ በምን አስቀድመህ አየኸው ይሉኛል ፡፡እኔ ግን አንዳንዴ የግል ውሳኔ ለመወሰን ከብዙ አቅጣጫ ተፅዕኖ ካልደረሰብን ለለውጥ የማንነሳሳ ወገኖች እንዳለን ከራሴ ተሞክሮ አረጋግ ጣለሁ፡፡ 7/9/2018 01:49:32 am
ይኄይስ አማረ ተሞክርህን ስላከፈልከኝ ከልብ አመሰግናለው። ይህንንም በምታገኘው ዕድል ሁሉ በማከፈል ለብዙዎች በረከት ሁን። አሁንም በጀመርከው ጉዞ እግዚአብሔር ይባርክህ።
Bekele Shanko
7/11/2018 07:12:55 am
ይህ መጣጥፍ በቡድንና በኅብረት በመሥራት ውስጥ ያለውን ኃይል ችላ ሳይል በኅብረት ውስጥ ያለውን የግለሰቦችን ሚና አጉልቶ ያሳያል። እያንዳንዱ ቤተሰብ አካባቢውን ቢያጸዳ ከተማችን የጸዳች ይሆናል እንደተባለው ሁሉ አገርን ለማሳደግ የእያንዳንዱ ግለሰብ እድገት፥ ኃላፊነትና አስተዋጽኦ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ያሳያል። እጅግ በጣም ጥሩ እይታ ነው። Comments are closed.
|
AuthorMiheret T. Eshete Archives
February 2023
Categories
All
|